አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ (ከ፲፰፻፷፬ እስከ ፲፱፻፴፯ ዓ.ም.)
ኪዳነ ወልድ ክፍሌ: የሕይወት ታሪክ
አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ በሸዋ ክፍለ ሀገር በይፋትና ጥሙጋ አውራጃ በ፲፰፻፷፬ ዓ.ም. ተወለዱ። ለትምህርት ሲደርሱ በአካባቢያቸው የነበረውን የአገራቸውን ትምህርት ተማሩ። በኋላም ወደ ጎንደር ተጉዘው የመጻሕፍትን ትርጓሜ አጠኑ። በጊዜው የነበራቸው የቀለም አቀባበል፣ የሚስጥር መመራመርና መራቀቅ በጉባኤው ላይ "የቀለም ቀንድ" የሚል ቅጽል ተሰጣቸው።ማናቸው ማናቸው
አለቃ ኪዳነወልድ ከግዕዝና አማርኛ ሌላ ዐረብኛ፣ ዕብራይስጥ፣ ላቲን፣ ሌሎችንም ቋንቋዎች አጠናቅቀው ያውቁ ነበር ። አለቃ ኪዳነወልድ በእየሩሳሌም ለ፳፪ ዓመት ተቀምጠዋል ። በዚህም ወቅት ብሉይና ሐዲስ በሦስት ቋንቋ ጠንቅቀው አመሳክረው ተርጕመዋል ። ኪዳነወልድ ክፍሌ በ፲፱፻፳፮ ዓ.ም. የመጀመሪያውን መዝገበ ፊደል አውጥተው ከልዩልዩ ቋንቋዎች ጋር በማመሳከር አሳትመዋል ። የኢትዮጵያ ፊደል አመጣጡንና ባህሉን በውል አስተባብረው በማቅረባቸውም በጊዜው ተቋቁመው ለነበሩት ትምህርት ቤቶች መመሪያና መማሪያ ለመሆን በቅተዋል ። ቀጥለውም ትንሽ አማርኛ ፊደል ከአረብና ከዕብራይስጥ አቆራኝተው አሳትመዋል ።
አለቃ ኪዳነወልድ በተለያየ ዘይቤ ያቀርቧቸው የነበሩት ግጥሞች ለትውልድ ታላቅ ጥቅም ይሰጣሉ ተብለው የሚገመቱ ናቸው ። እንዲያውም ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪቃ የብዙ ሺሕ ዘመናት ነጻ አገር ባለፊደልና ባለቋንቋ የሆነች እሷ ብቻ ስለሆነች ትውልድ ያገሩን ትምህርት በመጀመሪያ እንዲማር ያካሂዱት የነበረው ቅስቀሳ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ። በዓለም ስማቸው የገነነ የሥነ ጥበብ፣ የኪነ ጥበብ ፣ የጽሑፍ ባለአጉዛዎች የሚደነቁባቸው በራሳቸው ቋንቋ ጽፈው ለዓለም የአቀረቧቸው ሥራዎች ናቸው ይላሉ ።
አለቃ ኪዳነወልድ ለኢትዮጵያ ባላቸው ዐቅም በብሔራዊ ስሜት ተነሳስተው ለታሪክ የሚቀርቡ በርከት ያሉ መጻሕፍት ጽፈው አሳትመዋል ። በተለይም ከዘጠኝ መቶ ገጾች በላይ የሆነው "የሰዋሰው መጽሐፍ" ታላቅ እንደሆነ ይነገራል ። አለቃ ኪዳነወልድ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ታላቅ አስተዋፅኦ ያደረጉ ሰው ነበሩ ።
አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ በተወለዱ በ ፸፪ ዓመታቸው ፤ ሰኔ ፳፬ ቀን ፲፱፻፴፮ ዓመተ ምሕረት ዐርፈው ደብረ ሊባኖስ ተቀበሩ።[2]
ኪዳነ ወልድ ክፍሌ: ማመዛገቢያ
- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ፣ ብሔራዊ ቢብሎግራፊ (የደራሲያን አጭር የሕይወት ታሪክ) ፤ ፲፱፻፺፰ ዓ.ም. [1] Archived ጁላይ 20, 2011 at the Wayback Machine (ታኅሣሥ ፲፪ ቀን ፳፻፫ ዓ.ም. የተነበበ)